እድር ስንል ምን ማለታችን ነው?

ኢትዮጵያዊያን ከምንኮራባቸው ቅርሶቻችን መሀል የተለዩና የዳበሩ ባህላዊ ትውፊቶች ባለቤትነታችን ይገኝበታል። ከነዚህ ባህላዊ ሀብቶች መሀል ደግሞ በተለይም ዕቁብና ዕድር ልዩ መገለጫዎቻችን ናቸው። ዕቁብ ገንዘብ ነክ የሆኑ ችግሮቻችንን ለመቋቋም አበው የዘየዷት መላ ናት። ዕድር ግን መሰረቱ የሰፋ ፣ ፋይዳውም የላቀ እሴታችን ነው። ዕድር ስንል ስለግሩም ታሪክና ባህላችን ማውሳታችን ነው። ስለአብሮነት ፣ ስለመተሳሰብና ስለፍቅርም መዘከራችን ይሆናል። ማህበራዊና ስነልቦናዊ መላችንንም የሚያስታውስ ልዩ የማንነት መገለጫችንም ጭምር ነው። አንዳንድ የዋሆች ዕድርን ከቀብር ፈጻሚ ኢንሹራንሶች ጋር እያመሳሰሉት ይሞኛሉ። ጠቀሜታውንም ከአንዲት የጭንቅ ቀን ደራሽ ግልጋሎት ጋር ብቻ ሊያስተሳስሯት ይደክማሉ። ረጋ ብለው ቢያስቡት ግን ዕድርና ኢንሹራንስ ሁለት ከቶም የማይማሰሉ ተቋማት መሆናቸውን መረዳት አይገዳቸውም። ሁለቱ የተዋቀሩበት መሰረት የተለያየ ፣ የጠቀሜታቸው አድማስም ፍጹም የተራራቀ ናቸውና።
እድር በሲድኒ ለምን?

ባለፉት ዓመታት ውስጥ በሲድኒ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ ጨምሯል። ይህንኑ የነዋሪ መብዛት ተከትሎም በተለያዩ ሁኔታዎች በሞት የሚለዩን ወገኖቻችን ቁጥር ከፍ ማለቱ አልቀረም። ሞት በየትኛውም የዕድሜ ክልል ላይ ባሉ ሰዎች ላይ ሳይታሰብ ደራሽ የመሆኑ ዕውነት አሳሳቢ በመሆኑም በሲድኒ የምንኖር ኢትዮጵያውያን ችግሩን በጋራ የምንወጣበት ተቋም እንዲኖረን የግድ ብሏል።
ሲድኒ ሰፊ የቆዳ ስፋት ያላት ከተማ እንደመሆኗ ኢትዮጵያዊያን ነዋሪዎችም በአንድ አካባቢ ከመሰባሰብ ይልቅ በአብዛኛው በተለያዩ ስፍራዎች ተበታትነን ነው የምንኖረው። ከቦታ ርቀት አንጻርም እርስ በርስ የመገናኘቱም ሆነ አንዱ የሌላውን ችግር የመስማት ዕድሉ ከፍተኛ አይደለም። ይህን መሰሉ የግንኙነት መላላት ደግሞ በቀላሉ የሚታይ አልሆነም። በተለያዩ ጊዚያት በአባላት ቤተሰቦች ላይ የሞት አደጋዎች ሲደርሱ ዕድሩ አስፈላጊ ዝግጅቶችን ከማመቻቸቱም በላይ አባላቱ በስፍራው ተገኝተው በኅዘን የተጎዱ ቤተሰቦችን በማስተዛዘንና በማጽናናት ደራሽነታቸውን አሳይተዋል።
በወጪ ደረጃም በአጭር ጊዚያት ውስጥ ከ23 ሺ ዶላር በላይ በማውጣት የሞት ኅዘን ለደረሰባቸው አባላት ተገቢውን ክፍያ አከናውኗል።


የእኛው እድር ወይስ ኢንሹራንስ?

እኛና እነሱ
  • እርስ በእርስ መረዳዳትን ምርኩዝ ያደረገ፤
  • ለህግና ስርዓቱ ፍጹም ተገዢ ከመሆንም ባሻገር ለወገናዊና ባህላዊው ቁርኝቱ የቆመ፤
  • በአባላት ጉባኤ በሚታጩ ሙሉ ፈቃደኛ በሆኑ ተወካዮች በመግባባት፣ በመደማመጥ፣ በመቻቻል ግልጋሎት የሚሰጥ አስተዳደር ያለውና ከአባላት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ማድረግ የሚችል፤

  • ህልውናው ከአባላቱ ከሚያካብተው ትርፍ ላይ የተመሰረተ፤
  • ከቅድመ ማስጠንቀቂያ (ፖሊሲ) ውጪ ወልፈት በማይል እርዳታ ላይ ያነጣጠረ፤
  • ከቴሌፎን የማይዘልና በሚከፈለው ደመወዝ አስከፊነትና አስደሳችነት ላይ ስሜቱን በደበቀ የአስተዳደር ተወካይ ግልጋሎት የሚሰጥ፤
የእድር ማኅበራዊ ገጽታው ምን ይመስላል?

ጥናታዊ አባት እናቶቻችን የዕድርን ሀሳብ ሲጸንሱ ዓይነታውን ትኩረት ለማህበራዊ ፋይዳው የሰጡት ይመስላሉ። ‹ህይወትና ሞት› ህብር ፈጥረው የሚዘልቁ የተፈጥሮ ሂደቶች ናቸውና ከዕልፈት በፊት ህይወትን የማድመቁን አስፈላጊነት ከዕድር አወቃቀራቸው መረዳት አይከብድም። መተሳሰብ ፣ መረዳዳትና አብሮነት በዕድር ውስጥ ተሰናስለው የሚተገበሩ ረቂቅ ሀይሎች ናቸው። ዕድር ሀይማኖት ፣ ዘር ፣ የፖለቲካ ዕምነትና የኑሮ ደረጃ ልዩነትን ጥሶ ፤ በአባላት ልቦና ውስጥ ‹ለችግርህ ደራሽ ነኝ› ፣ ‹በጭንቅሽ ጊዜ ከጎንሽ ነኝ› የሚል ጠንካራ የፍቅር መንፈስ የሚያስተላልፍ ተቋም ነው። በመንፈስ የሚያስተሳስር ኃያል ገመድ። መራራቅን የሚያከሳ ፣ መጨካከንን የሚያመክን ቅን መሰረት። . . .


ከስነ-ልቦና አንጻር ያለው ድጋፍ ምን ይሆን?

ምዕራባዊያን ስለዕድር አያውቁም። ወይም በዕድር አይገለገሉም። ክፉ ቀን ሲመጣ የቀብር ኢንሹራንስ አለልን ይላሉ። መሪር ሀዘናቸውን የብቻ አምቀውት ስለሚቆዩም ለስነ-ልቦና ችግር የሚጋለጡበትን ዕድል ያሰፋሉ። ምናልባትም በዚህ ሳቢያ ሳይኪያትሪስት ቢሮ ለመመላለስ ይገደዱ ይሆናል። እኛ ግን ዕድር አለልን። ያቺ ክፉ የጭንቅ ቀን ደርሳ ‹የኔ› የምንለውን የቤተሰብ አባል ስናጣ፤ ‹አይዞን! አለሁ› ባያችን ብዙ ነው። መሪር ሀዘናችንን ተካፍሎ ከጎናችን የሚቆም ፣ ያጣነውን ‹ውድ› ሰው በክብር አጅቦና በውጉ አልቅሶ የሚሸኝ ወገን መኖሩ ከፍተኛውን መጽናናት ይሰጠናል። ከቀብር እስከማስተዛዘን ከጎናችን የማይለዩት አባላት ጥልቁን ሀዘናችንንና ስጋታችንን ለመክፈል ልዩ አለኝታ ይሆኑናል። በተለይም ለእንደኛ ዐይነቱ ከወዳጅ፣ ዘመድ-አዝማዱ ተለይቶና ከትውልድ አገሩ ብዙ ሺ ማይልስ ርቆ ለሚኖር ሰው፤ የቤተሰብ አባልን በሞት መነጠቅ በዋዛ የማይቋቋሙት መሪር መከራ ነው የሚሆንበት። ያለአጋር ፣ ያለወገን የማይወጡት ፈተና። “ለሰው መድሀኒቱ ሰው ነው” እንዲሉ።


ባህላዊ ትስስር አለውን?

ከዕድር ፋይዳዎች አንዱ ከማንነታችን ጋር ያለው ቁርኝት ነው። ኢትዮጵያዊያን ከበርካታ ክፍለ ዘመናት አስቀድሞ መላ ብለው ያበጇቸው የአኗኗር ዘይቤዎች ባህል ታሪኮቻችን ናቸው። ዕድር ደግሞ ከነዚህ አንዱ ነው። የመከራን ቀን የተሻገሩበት ፣ ተጋግዘውና ተሳስበው ፈተናን ያለፉበት ፍቱን መላ። በዚህ ድንቅ እሴታችን ውስጥ የማንነታችን አሻራ አለ። አንዳችን የአንዳችን አለኝታ የመሆናችን ልክ ፤ የመደራረስ ፣ የመደጋገፋችን ዕውነት የሚገለጥበት አሻራ።. . . ልንጠብቀው ፣ ልናከብረው የሚገባን አኩሪ ቅርስ። ይህን ድንቅ እሴት መጠበቁ ማንነትን የማስጠበቅም ጉዳይ ነው ። ከአገራችን ብንርቅም አገራችን ግን ከውስጣችን እንዳትርቅ አጥብቆ የመፈለጋችን መገለጫ ነው ማለት ይቻላል። ይህም ታላቅ የልብ ኩራት ይሰጣል።


ኢኮኖሚያዊ ድጋፉስ ምን ያህል ነው?

ህይወት ውብ ነችና ስለሞት ማሰብ ያስጠላል። ብዙዎቻችን ያቺ ክፉ የመለየት ዕለት አንድ ቀን መምጣቷ እንደማይቀር እንኳ ትዝም አይለንም። በዚህ ምክንያት ‹ድንገት የቤተሰቤ አባል ቢሞት የሚጠብቀኝ ወጪ አለ› በሚል ለብቻ የምናስቀምጣት ወረት ላትኖረን ትችላለች። በአለንበት አገር ደግሞ የቀብር ማስፈጸሚያ ወጪው ከፍተኛ ነው። የአስከሬን ማቆያው ፣ የመቃብር ስፍራው ፣ የመኪና ኪራዩ፣ የአበባውና . . . ሌላም ሌላም። እንደዋዛ ንቀን የማናስበው ይህ የክፉ ቀን ወጪ ዳጎስ ያለ በመሆኑ በተለይ ላልተዘጋጀበት ሰው በመሪር ሀዘኑ ላይ ተጨማሪ ድንጋጤና ጭንቀት የማሳደር ጉልበት አለው።